እስከ መቼ ድረስ ወያኔ ይጫወትብን?

በሽፋን ስሙ ኢሕአዴግ ተብዮው ወያኔ/ሕወሐት ዕድሜውን ለማራዘም ይመቸው ዘንድ በውስጣችን ቅራኔን በማስፋት በዘር እያደራጀ፤ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ሕዝብን በእሥራት፥ በግድያ፥ በበሽታ፣ በረሐብ እየፈጀና እያስፈጀ ፋሽስታዊ ሥርዓቱን ከጫነብን ሓያ ዓመት በላይ አልፎናል። የተቃዋሚው ጎራም ባልረቡ ልዩነቶች እርስ በርስ ባለመግባባትና ተለጣፊውም በዝቶ ትግላችን ግብና ዓላማውን ከመሳቱም አልፎ ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ አስፈራርቶና አሽብሮ ለመግዛት በሚያደርገው ትግል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ድጋፍ እያበረከትን ነው።

ድክመቶችን መጠቆሙ ‘ብዬ ነበር’ ለማለትና አንዳችን በሌላው ጣት ለመጠንቆልና ለማስጠንቆል ወይም ቅራኔዎችን እያሰፉ የሚመለከቱንን ጉዳዮች ጭራሽ ላለማውሳት፥ ወይም በፖለቲካ ለመወንጀልና ለማስወንጀል ሳይሆን እንደ ሰለጠነ ዜጋ በችግራችን ዙሪያ መደራደርና መወያዬት ይቻል ይሆን? በማለት ነው። ከብዙ በጥቂቱ  ……

1ኛ/ ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው ያለጋራ ተሳትፎ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች በአንድ ፓርቲ፥ ግንባር፥ ወይም ንቅናቄ የትግል ስልት ብቻ መፍታት የማይቻል በመሆኑ ወደ አንድ መደራደሪያ ዙሪያ ያለመምጣትን በተመለከተ፣

2ኛ/ ድርጅቶች ለፖለቲካዊ ችግሮቻችን መፍትሔ በሚሆኑ ሐሳቦችን መቀበልና መስጠትን ያለመቻቻል፥

3ኛ/ በዋነኛነትና በመለስተኝነት መምጣትና መፈታት ያሉበትን ችግሮች ቅደም ተከተልን በተመለከተ፤ ለምሳሌም ዋነኛው የኢትዮጵያ ጠላት ወያኔ በመሆኑ በቅድሚያ ትግሉ ኢላማ ማድረግ ያለበት በወያኔ ላይ ሲሆነ እርስ በርስ መጠላለፉንና መደናቆሩን ማቆም በተመለከተ፣

4ኛ/ በጋራ የመሥራት ተለምዶ ማጣት፥

5ኛ/ ፓርቲዎች ያለመተማመንና የሥልጣን ጥማት፥

6ኛ/ ለአንድ ፓርቲ የዲሞክራሲ መሰረቱ የጎሳ ነጻነት ሳይሆን የግለስብ ነፃነት መሆኑን ያለማወቅ፤ ለምሳሌ አማራ፥ ኦርሞ፥ ትግራይ… ወዘተ እያሉ በዘር ማደራጀቱ በነጻነት አብሮ መኖርን ዜጎች በነጻነት ከክልል ወደ ክልል  መንቀሳቀስን የሚወስን መሆኑን ያለመረዳት፥

7ኛ/ ከወያኔ በተወረሰው መጥፎ ፈሊጥ የዘር ፓርቲ፥ ግንባር ወይም የጎሳ ነፃ አውጪ ነኝ ባይነት ከማን ለማን? ወዴትስ ይወስደናል ብሎ እራስን ያለመጠየቅ፥

8ኛ/ የተቃዋሚ ስም ይዘው በአመራር ድክመትና በጊዜያዊ ጥቅም  ኢትዮጵያን ለወያኔ የሰጡ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድክመታቸውን አምነው ወደ ኋላ ተመልሰው የፓርቲያቸውን ፕሮግራምና አመራራቸውን ያለመገምገም፣

9ኛ/ ሳያውቅ ፖለቲካ አዋቂ ነኝ ባይነት መብዛቱ። መማማርን ያለመቻል፥

10ኛ/ ጎሰኝነት ወይም አንዱ ዘር ሌላውን ዘር መናቅ፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ዘር አጥንትና ደም ተከፍሎባት የተጠበቀች መሆኑን መርሳት።

ከኢትዮጵያ ቤተሰብ በመምጣታችን ብቻ ሳይሆን በምድሯ በመወለዳችን ጭምር ከአፈሯ፣ ከባሕሏ፣ ከታሪኳና ከነጻነቷ፣ በደማችን፣ ከማንነታችንና ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተዋሃድን ስለሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሩ ችግራችን፥ ደስታው ደስታችን በመሆኑ ዛሬ በአደጋ ላይ ላለው ወገኖቻችን ደራሽ እኛው ዜጋዎቿ ብቻ በመሆናችን፤ ወያኔን የሚቃወሙ ድርጅቶች ሁሉ አንዱን ከአንዱ ሳንለይ በሞራል፣ በጉልበት ሆነ በገንዘብ መደጋገፍ “ኢትዮጵያን አድን” አደራና ግዴታ የሁሉም መሆን አለበት። በተቃዋሚው መሐል የሚፈጠሩ ጥቃቅን ልዩነቶች እንደ ዋነኛ ምክንያት ሆነው መታየት የለባቸውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር በትከሻችን ላይ በመሆኑ ሁላችንም በጥፋትዋ ላይ ዝምታ በታሪክ ያስጠይቀናል። አባቶቻችን መስዋዕትነትን ሳይከፍሉ አገራችን እንዳልቆየች ሁሉ ዛሬ ከማናችንም እንደ ችሎታችንና  እንደየአቅማችን መስዋዕትነት ይጠበቅብናል።

የወያኔ ፖለቲካዊ መጨቆኛና የአንድ ጎሳ ቅኝ አገዛዝ መሳሪያ የሆነው  የአዲስ አበባው አጋቹ ፍርድ ቤት በስመ አሸባሪነት ሞትና የዕድሜ ልክ እሥራት በንጹሐን ኢትዮጵያውያን ላይ በየጊዜው መፈረጁ የፖለቲካ ቲያትር ከመሆኑም አልፎ ጦርነት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ መክፈቱን በግልፅ እያየን ነው። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በወያኔ/ሕወሐት እስር ቤት ናቸው። በወያኔ መንግሥት ስብዕና ክብርና ቦታ የሌለው በመሆኑ የሕሊና እስረኞች ወያኔ ለፈጠረው ፖለቲካዊ ችግሮች መስዋዕትነትን እየከፈሉ ናቸው።

የትግራይ ሕዝብ ትናንት የኢትዮጵያ ታሪክ ግንባታ ማዕከል እንደ ነበርክ ሁሉ ዛሬ አንድነታችን ለማፍረስ በአንተ ስም በሚነግዱ በወያኔ የተጫረው እሳት እየፈጀን በመሆኑ ከኢትዮጵያ ወገኖችህ ጎን በመቆም በወያኔ መንግሥት ላይ ክንድ በማንሳት አንድነታችን ለማስጠበቅ ቅድመ  ግዴታህን መወጣት በጥብቅ ይፈለግብሃል። ወያኔ ከደደቢት በረሃ ተነስቶ አዲስ አበባ ገብቶ በመንገሥ በአባቶቻችን መስዋዕትነት ተከብሮ የቆየውን ድንበራችን በማፍረስ፣ ከቤቶቻችን በማፈናቀል፣ መሬታችንን ለባዕድ በመስጠት ያደረሰብን በደል ጣሊያን ከአውሮፓ በመምጣት በቃጣብን ወረራ ካደረሰብን ጉዳት በልጦ ይገኛል። ወያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዕራብ እያለቀ ከውጭ አገር የመጣውን የዕርዳት እህል ለማግኘት የወያኔ ደጋፊ መሆን አለብህ/ሽ የሚል ፖሊሲ የሚያራምድ ጨካኝና ጎጠኛ መንግሥት ነው። በዚህ አጋጣሚ የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑ ለምሳሌ እንደነ ኃይለማርያም ደሳለኝ ያሉ የወያኔ ሥርዓት አራማጆችና ጉርሻ ተቋዳሾች ከወያኔ እኩይ ተግባር በመላቀቅ ከራሳችሁ ጊዜያዊ ጥቅም የመላ ኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም በማስቀደም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመሰለፍ ከታሪክ ግድፈት እጃችሁን አጽዱ እንላለን። አለበለዚያ ጠ/ሚኒስቴር ኃይለማርያም የቀድሞ ወያኔ ታጋዮችን የበላ ሞት እንደምንዣበብቦትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጣና ፍርድም እንደሚጠብቅዎት አይዘንጉ። “የራስዋን ልጅ የበላች ድመት ለዶሮ ጫጩት አትሳሳም” እንዳሉትም እንዳይሆን እንመኝሎታለን።

የወያኔ ሥርዓት ኢትዮጵያዊነትን በጎሳ ሸንሽነህና ከፋፍለህ ግዛ በመሆኑ በተለይም አንድነታችን  ከሚያናጉ በርካታ ፈርጆች ጥቂቶቹ በሐይማኖትና በድንበር መሬት ግጭቶችን መፍጠርና ደም ማቃባትና የኢትዮጵያን መሬት ቆርሶ ለባዕድ መስጠት፥ ዜጎችን ማሰር፥ መግደልና ማፈን ዋነኛዎቹ ናቸው።

አንድ ጀግና አባት ሰለ አገር ምንነትን እንዲህ ይላሉ ..  አገር በታሪክ፣  በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በልማድ፣ በተስፋ፣ በደስታና በመከራ ተሳስሮ የሚኖር አንድ ወገን የሆነ ሕዝብ የሚኖርበት የዓለም ክፍል ነው። አገር ማለት፤ አያት ቅድመ አያት የተወለዱበት፤ አድገው በጀግንነት ከውጭ ጠላት እየተከላከሉ፥ ለሕዝብና ለመንግሥት የሚጠቅም ሥራ ሠርተው ዕድሜያቸው ሲደርስ ልጆቻቸውን ተክተው የተቀበሩበት ምድር ነው። በመወለድ እትብት፤ በመሞት አካል ከአፈሩ ጋር ስለሚዋሐድ፤ የአገሩ አፈር ሕዝቡ በላዩ የሚኖርበት ማለት ነው። እግዚአብሔር ከምድሯ ፍሬ ሕይወት እንዲገኝባት በማድረጉ አገር እያጠባች የምታሳድግ ፍቅርዋ በአጥንትና በሥጋ ገብቶ የማይደመሰስ የሆነች እናት ማለት ነው። ከልጅነት ጀምሮ ወንዙ ተራራው ሜዳው ቆላውንና ደጋውን በማየት ስላደግን አባቶች በሕይወትና በሞት የሠሩበት ደግ ሥራ በአእምሮ ታትሞ ስለ ቀረ በአገር እስካሉ ሲታይ በስደት ሲሆን ሲታሰብ ፍቅርና ናፍቆት የሚያሳድር አገር ነው። አገር አባት እናት ዘመድ ምግብ ጌጥና ሀብት በመሆኑ ድህነትና ጥቃት በመጣ ቁጥር እስከ ሞት ድረስ እንዲሠራበት ከአያት ከቅድመአያትና ከአባቶች በጥብቅ የተሰጠ ያደራ ገንዘብ ነው። ይላሉ።

በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣት በወያኔ በሩ የተዘጋ በመሆኑ፤ ማናችንም በሰላማዊ መንገድ ሆነ በአመጽ በሩን ለማስከፈት የመረጥነው መንገድ እንደምክንያት ሆኖ ሳያከፋፍለን ወያኔም ይህንን ምርጫችን ምክንያትም አድርጎ በቅራኔው ላይ ሳያካብት ነቅተን መገኘት አለብን። ዛሬ በማናቸውም ምክንያት ነጥሎ ውድ የኢትዮጵያ ልጆችን  በሞትና በእድሜ ልክ እሥራት ወያኔ መፈረጁ ነጌ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ዕጣ ፋንታ በመሆኑ በተቻለን አቅም ወያኔን ለማጋለጥና፥ ትግሉን በሁሉም መስክ  ለማፋፋም ቅድሚያ ወጣቱ መጫወት አለበት። ምክንያቱም የወያኔ መንግሥት የአሸባሪዎች፣ የአፋኞች፣ የገዳዮች፣ የአፈ ጮሌዎችና የተራ አጭበርባሪዎች መንግሥት ነውና።

ሞት ለወያኔ!!

ደመላሽ ካሳ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *